Pernkopf Topographic Anatomy of Man!

“ዶክተር ሱዛን ማኪነን ቀዶ ጥገና ማድረግ ሲያሻት እጇን ወደ አንድ የቀደመ መፅሐፍ ትዘረጋለች፤ በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ የተፃፈ መፅሐፍ።”

መፅሐፉ የሰው ልጅ ሰውነትን ልክ እንደ አንድ የኤሌክትሮኒክስ እቃ ከፋፍሎ ያሳያል፤ ከቆዳ ጀምሮ እስከ አጥንት፤ ከጉበት እስከ አንጅት መፅሐፉን ስስ ልብ ያላቸው እንዲያዩት አይመከረም።

መፅሐፉ ‘Pernkopf Topographic Anatomy of Man’ የተሰኘ ርዕስ አለው። የሰው ልጅ መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ ተብሎ በግርድፉ ሊተረጎም ይችላል፤ ወይም መልክዓ-ሰዋዊ አቀማመጥ።

ይህን መፅሐፍ የቀዶ-ጥገና ሐኪሞች እንደ ቅዱስ መፅሐፍ ነው የሚያዩት ተብለው ይታማሉ። የሰው ልጅን ውስጣዊ አሠራር ብትንትን አድርጎ የሚያሳየው መፅሐፍ ኤድዋርድ ፐርንኮፕፍ በተሰኘ የኦስትሪያ ሰው የተፃፈ ነው።

መፅሐፉ አሁን ከህትመት ውጭ ቢሆንም ማግኘት ግን ብዙ ድካም አይጠይቅም። በይነ-መረብ ላይ የተለያዩ የመፅሐፉ ዕትሞች ይገኛሉ። ከእርስዎ የሚጠበቀው ትንሽ ሺህ ፓውንዶች (ረብጣ ብር) መያዝ ነው።

መፅሐፉ ያላቸው ሰዎች ግን በኩራት ሼልፋቸው ላይ ወይም ከመስታወት ሥር ሲያስቀምጡት አይታዩም፤ ምክንያቱ ወዲህ ነው። ይህን መፅሐፍ ለመፃፍ የሰው ሕይወት ተከፍሏል-የሺህዎች ሕይወት።

መፅሐፉ ላይ ደም-ሥራቸው፣ አጥንታቸው እና ቆዳቸው እንደ ምስር ተለቅሞ የሚታዩ ሰዎች በናዚ ግፍ የተጨፈጨፉ ናቸው። ሐኪሞች ይህን መፅሐፍ በፍፁም ሊጠቀሙበት አይገባም የሚሉ በርካቶች ናቸው። ምክንያታቸውም ‘መፅሐፉ ጥቁር ታሪክ አዝሏልና’ ይላሉ።

ዶክተር ሱዛን መፅሐፉን መጠቀሟ ሰላም እንደማይሰጣት ባትክድም ለሥራዋ እጅግ አጋዥ እንደሆነ ግን አትሸሽግም።

ከናዚ የጅምላ ጭፍጨፋ (ሆሎኮስት) የተረፉት የጤና ፕሮፌሰሩ ዮሴፍ ፖላክ ‘መፅሐፉ የሞራል ጥያቄ ያለበት ነው’ ይላሉ። «የመፅሐፉ ሥረው-ግንድ ሠይጣናዊ ተግባር ቢጠናወተውም አሁን ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ለበጎ ነው።»

የመፅሐፉ ደራሲ ኤድዋርድ ፐርንኮፕፍ የናዚ ዶክተር ነበር፤ የአዶልፍ ሂትለር ቀንደኛ ደጋፊ። የሥራ ባልደረባዎቹ ‘ሶሻሊስት’ ሲሉ ይገልፁታል፤ ወደ ሥራ ሲመጣ የናዚ ምልክት ክንዱ ላይ የማይለየው ቀንደኛ ናዚ ነበር።
ግለሰቡ በቪዬና ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሆኖ ሲሾም የሎሪየትነት ሽልማት ያገኙትን ሳይቀር አይሁዶችን መርጦ ጠራርጎ ያባረረ ሰው።

በወቅቱ በናዚ የተገደሉ የአይሁዶች ሬሣ ለሕክምና ትምህርት ወደ ዶክተሩ ይመጡ ነበር። ሰውዬው በቀን 18 ሰዓት የሰውን ልጅ አካል ሲቀድ እና ሲሰፋ፤ ሲከፋፍል ይውላል።

አጋሮቹ ደግሞ ያዩትን በፎቶ እና በስዕል ያስቀራሉ። አንዳንድ ጊዜ ክፍሉ ሙሉ ከመሆኑ የተነሳ ሊገደሉ ተራ የተያዘላቸው አይሁዶች አንድ ቀን ይራዘምላቸው ነበር።

መፅሐፎች የመጀመሪያ ዕትሞች የናዚ ምልክት ያለባቸውና ፊርማ ያረፈባቸው ናቸው። 1964 (በግሪጎሪ አቆጣጠር) እንግሊዝ ውስጥ የታተመው ሁለተኛ ዕትምም ሲሆን የናዚ ምልክት ፊርማ ሰፍሮበታል።

90ዎቹ ላይ የሕክምና ተማሪዎች መፅሐፉ ላይ ያሉ ሰዎች እነማ ይሆኑ የሚል ጥያቄ ይጫርባቸውና መመርመር ይጀምራሉ። በኋላ ላይ የመፅሐፉ ያለፈ ምስጢር ሲጣራና ሲታወቅ እንዳይታተም እግድ ተጣለበት።

መፅሐፉ በበርካታ ሃገራት ከጥቅም ውጭ እንዲሆን ተደርጓል። በታሪክነት እንዲቀመጥ እንጂ ሐኪሞች እንዲጠቀሙበት አይመከርም። ነገር ግን በቅርቡ የቀዶ ጥገና ሐኪሞች የተሳተፉበት ጥናት ተሠርቶ 59 በመቶ ያህሎቹ መፅሐፉን እንደሚያውቁት ሲናገሩ፤ 13 በመቶዎቹም እንደሚጠቀሙበት ይፋ አድርገዋል።

ዶ/ር ሱዛን የዚህን መዘዘኛ መፅሐፍን ያህል ቅንጣት ታክል እንኳ መረጃ የሚሰጥ ሌላ መፅሐፍ የለም ትላለች። በተለይ ደግሞ ከበድ ያሉ ቀዶ ህክምናዎችን ቀለል የሚያደርግ እንደሆነ ዶክተሯ ትመሰክራለች።

ዶ/ር ሱዛን በአንድ ሰው ላይ የቀዶ ህክምና እያካሄደች ነበረች። እግሩ አካባቢ ጉዳት የደረሰበት ይህ ሰው ትክክለኛው ነርቭ ተገኝቶ ጥገና ካልተደረገለት እግሩ ሊቆረጥ ግድ ነበር።
ዶክተሯ ወዲህ ብትል ወዲያ ትክክለኛው ነርቭ ሊገኝ አልቻለም። በስተመጨረሻ ግን እጇን ዘረጋች. . .ወደ መፅሐፉ። የሰውየውም እግሩ ከመቆረጥ ዳነ።

ፐርንኮፕፍ ናዚ ከተሸነፈ በኋላ ለእሥር ቢበቃም ከሦስት ዓመታት በኋላ ተለቀቀ። ምንም ዓይነት ክስ አልተመሠረተበትም ነበር።
ሰውዬው ከእሥር ከወጣ በኋላ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዕትም በማውጣት ቸብችቧል። አራተኛውን ዕትም ሊያወጣ በመዘጋጀት ሳለ ነበር ሞት የቀደመው።

መፅሐፉ ከወጣ 60 ዓመታት ቢያልፉትም አሁንም የሰው ልጅ ሰውነትን ለማጥናት ወደር የማይገኝለት እየተባለ ነው። መፅሐፉን የመጠቀም ተገቢነት ግን አሁንም አከራካሪነቱ ቀጥሏል።

ኤድዋርድ ፕርንኮፕፍ

2 thoughts on “Pernkopf Topographic Anatomy of Man!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *