Christ’s Crucifixion: An Examination by Medical Science

ስቅለተ ክርስቶስ፡ በሕክምና ሳይንስ ሲዳሰስ

ይህ ጽሑፍ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእለተ ሐሙስ ማታ ጀምሮ እስከ እለተ ዓርብ ፍጻሜ ስቅለቱ ድረስ ያሉትን ኩነቶች ከወንጌል እየተመለከተ በሕክምና ሳይንስ መነጽርነት አብጠርጥሮ ይመረምራል፡፡ ጽሑፉን የጻፍኩት የዛሬ ሁለት ዓመት ቢሆንም፥ በየጊዜው ከሚወጡ መጽሐፍት እና የምርምር ውጤቶች አንጻር በመከለስ እንዲዳብር አድርጌዋለሁ። ጽሑፉ ቢረዝምም፥ የጌታችንን የስቅለት ህማም በሚገባ ለመረዳት ይጠቅማልና፥ ታግሳችሁ ብትጨርሱት ብዙ ታተርፋላችሁ።

❶ መግቢያ

በዓለማችን የለውጥ ሞገዳቸው ቀዬዎችን፣ ደሴቶችን፣ ሀገሮችን፣ አህጉሮችን እንዲያውም መላው ዓለምን እስከማናወጥ የደረሰ ብዙ ታሪክ ቀያሪ ሰዎች በተለያየ ጊዜና ወቅት ተነስተዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች በአስተሳሰብ፣ በሞራል እሴት እና ሩቅ በመራመድ ከሌሎች ልቀው በመገኘታቸው ዓለምን እየቀየሩ በብዙዎች ደግሞ ተጠልተዋል፡፡ ሆኖም ግን ከእነዚህ ሁሉ ፍጹም የተለየ፣ እስከዛሬ ድረስም በሚሊዮኖች ልብ ውስጥ ነግሦ የኖረና ከሁሉም የላቀ አንድ ሰው አለ፤ እርሱም ፍጹም አምላክ ጭምር ነው፡- ኢየሱስ ክርስቶስ!

የኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር መምጣት ግን ከሌሎች ዓለምን ከለወጡ ሰዎች ጋር ሲነጻጸር ብዙ የሚለየው ነገር አለ፡፡ የእርሱ መምጣት ለዘመናት በጉጉት ሲጠበቅ የነበረ፣ ዘመን ሲታሰብለት፣ ሱባኤ ሲቆጠርለት፣ ነቢያት እና ነገሥታት ሲጠብቁት የነበረ ነው፡፡ ለዘመናት ዓለምን ሲያስጨንቅ የነበረ የኃጢያት ፍዳ መፋቅን ዓለም ሁሉ በተስፋ ይጠብቀው ነበርና፤ የተቆጠረው ሱባኤ ባለቀ ጊዜ በምድር ላይ ተወለደ፡፡ ከውልደቱ ጀምሮም ሕይወቱ ሁሉ በተዓምራት የተሞላ ነበር፡፡ መወለዱ በኮከብ ተጠቁሞ የሩቅ ሀገር ጥበበኞች መጥተው የሰገዱለት፣ የሥልጣኑ ተጋፊ እንደመጣበት ባመነ ንጉሥ ደም ጥማት የተነሳ በእናቱ እቅፍ ሆኖ የተሰደደ፣ የዓለም ሁሉ መጋቤ ሆኖ ሳለ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ፣ ዘመንን የሚያስረጅ ኃያል ሆኖ ሳለ በአንዴ ልደግ ሳይል በጥቂት በጥቂቱ ያደገ ነው፡፡ በልጅነቱ በምኵራብ ሆኖ ከአይሁድ ሊቃውንት ጋር ሲወያይ ፍጹም ይደመሙበት ነበር፡፡ ልጅ እንደመሆኑ የፈጠራትን ግን የወለደችውን እናቱን እየታዘዛት እና እያገለገላት አደገ፡፡ ሆኖም ግን የሚያስተምርበት ጊዜ በአስደናቂው ትምህርቱ ብዙዎች የተከተሉትን ያህል አስቀድሞ እጁን ዘርግቶ ሊያድናቸው የፈለጋቸው እና የጠበቃቸው ሕዝቦቹ ግን ሊከተሉት አልወደዱም፡፡ በመጨረሻም እንዲገረፍ፣ እንዲሰቀል እና እንዲሞት አስፈረዱበት፡፡

ይህ ጽሑፍ የኢየሱስ ክርስቶስን ሕማም እና ስቅለት ከሕክምናው አንጻር ይተነትናል፡፡ አሰቃቂነቱ ሲጎላ – ለአእምሮ የሚከብድ በሆነም ጊዜ ለዓለም የተከፈለውን ድንቅ ዋጋ ማስታወሻ ይሆናል፡፡

❷ ሐሙስ ማታ

2.1 በይሁዳ ተላልፎ መሰጠቱ

በወንጌል ተጽፎ እንደምናነብበው ከሆነ፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጌተሴማን በጭንቅ ሆኖ ከጸለየ በኋላ ከዋለበት እየዋለ እና ካደረበት እያደረ ከርሱ ጋር ለሦስት ዓመታት አብሮ የነበረው የአስቆሮቱ ይሁዳ የካህናት አለቆች እና የሕዝብ ሽማግሌዎችን እየመራ መጥቶ አሳልፎ ሰጥቶታል፡፡ በማቴዎስ ወንጌልም “ይህንም ሲናገር ÷ እነሆ ÷ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ” [ማቴ 26፡36] በማለት ይገልጸዋል፡፡ ይሁዳ ከኋላው መጥፎ ታሪክ የነበረው፣ በተጨማሪም ደግሞ ከሰዎች ይሰበሰብ ከነበረው ሙዳዬ ምጽዋት የሚሰርቅ ሌባ የነበረ ቢሆንም[1]፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የይሁዳን ሌብነት እያወቀ ጭምር ‹ገንዘብ ያዥ› አድርጎት ነበር፡፡ ሆኖም ግን በዚህ ደረጃ እምነት ቢሰጠውም፣ በነበረው ከፍተኛ የገንዘብ ፍቅር የተነሳ እምነቱን አፍርሶ ጌታውን ሊሸጥ ችሏል፡፡

ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የነበረ ተከታዩ እምነቱን አፍርሶ ለሠላሳ ዲናር አሳልፎ ጌታውን መሸጡ ሳያንሰው፣ አሳልፎ የሰጠው የሰላምና ፍቅር ምልክት በሆነው የመሳም ሰላምታ ነበር፡፡ ወንጌላዊው “አሳልፎ የሚሰጠውም÷ የምስመው እርሱ ነው፤ እርሱን ያዙት ብሎ ምልክት ሰጥቷቸው ነበር” በማለት ገልፆታል፡፡ የይሁዳ እምነት ማፍረስ እንዳለ ሆኖ፤ አብረውት የነበሩት ደቀ-መዛሙርት ሁሉ ትተውት መሸሻቸው ደግሞ ትልቅ ሥነ-ልቦናዊ ሕመምን ያጭራል፡፡ ቅዱስ ማቴዎስም ራሱን ጨምሮ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ “ከዚህም በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ” [ማቴ 26፡56] ብሎ ጽፏል፡፡ በሥነ-ልቦና ሳይንስ ውስጥ የቅርብ ሰዉ ክህደት ከሚያስከትሉት ነገር አንዱ ጥልቅ የሆነ የስሜት ጉዳት [Deep Emotional Pain] አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ በተለይም በራሱ የቅርብ ደቀ-መዝሙር እጅ ተላልፎ መሰጠቱ እና የሌሎቹ ደቀ-መዛሙርቶችም እርሱን ትቶ ከአጠገቡ መሸሽ ቀድሞ ከነበረበት ሁኔታ ላይ ተደምሮ ሊያስከትል የሚችለውን ኃዘን እና የስሜት ጉዳት ለመገመት አያዳግትም፡፡

2.2 ከባድ እና ረጅሙ የእግር ጉዞ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በይሁዳ እጅ ተላልፎ ከተሰጠ በኋላ ከደብረዘይት ተራራ ሥር ከሚገኘው ጌቴሴማን ከተሰኘው የአትክልት ስፍራ ለፍርድ ወደ ሊቀ-ካህናቱ ቀያፋ ተወስዷል፡፡ ይህንንም ደግሞ ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ ሲነግረን “ጌታችን ኢየሱስን የያዙትም ጻፎችና ሽማግሌዎች ወደ ተሰበሰቡበት ወደ ካህናቱ አለቃ ወደ ቀያፋ ወሰዱት፡፡” [ማቴ 26፡57] በማለት ነው፡፡ በዚህም ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጸሎትና በስግደት ሆኖ ሲጸልይበት ከነበረበት ቦታ – ማለትም – ከከተማ ወጣ ብሎ ከሚገኘው ጌቴሴማን በእግሩ እየተጓዘ ወደ ከተማው በመዝለቅ “አስቀድመው ከሐና ዘንድ ወሰዱት” [ዮሐ 18፡13]፡፡ ከዚህም ቀጥሎ ደግሞ የሐና አማት ወደነበረው ሊቀ-ካህኑ ቀያፋ ወዳለበት በእግሩ እንዲጓዝ ሆኗል፡፡ በወንጌል ትርጓሜም ከአንዱ ወደ አንዱ እየወሰዱ ያንከራተቱትን ሲገልጸው “እንደ ጎንባሲት ያለች ደጅ አለቻቸው፡፡ አንድ ጊዜ በአንዱ ሲያገቡት አንድ ጊዜ በአንዱ ሲያወጡት ሲያመላልሱት አድረዋል፡፡”[2] በማለት ነው፡፡

ምሽቱ በነጋም ጊዜ ማንከራተቱን ቀጥለውበታል፡፡ ሐዋርያው ማርቆስ ሲገልጸውም “በነጋም ጊዜ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቆች የሕዝቡም ጻፎች ሸንጎውም ሁሉ ተማከሩ፡፡ ኢየሱስንም አሠሩት፤ ወስደውም ለጲላጦስ ሰጡት፡፡”[ማር 15፡1] ተብሏል፡፡ ሆኖም ግን መንከራተቱ በዚህ ሳያበቃ ጲላጦስ ደግሞ ኢየሱስ ‹ገሊላዊ› መሆኑን በሰማ ጊዜ “ከሄሮድስ ግዛት ወገን እንደሆነ አውቆ ወደ ሄሮድስ ላከው፡፡”[ሉቃ 23፡7] — ሄሮድስ ግን “ሄሮድስም ከሰራዊቱ ጋራ ናቀው፤ ዘበተበትም፤ የጌጥ ልብስም አልብሶ ወደ ጲላጦስ መልሶ ሰደደው፡፡”[ሉቃ 23፡11]፡፡ እንግዲሀ እስካሁን ድረስ ጌታችን የተንከራተተው ሁሉ አንድ ላይ ደምረን፣ በወቅቱ ከነበረ የከተማው ካርታ ጋር አነጻጽረን ርቀቱን ስንለካ ኢየሱስ ክርስቶስ ከግርፋቱ በፊት 4 ኪሎ-ሜትር [2.5 ማይል] ያህል ርቀትን በእግሩ ተጉዟል፡፡ [3]

❸ የዕለተ ዓርቡ ሕማም

3.1 በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የደረሰው ግርፋት

የሳይንስ ጥናት ከስሜት ጋር ራስን ለያይቶ በአመክንዮ ብቻ መረጃዎችን መመልከት እና መመርመርን ይጠይቃል፡፡ ሆኖም ግን አልፎ አልፎ የሳይንሱ ጥናትም ቢሆን የሚያወጣው እና የሚያጎላው መረጃ እጅግ ሰቅጣጭ ከመሆኑ የተነሳ ከባድ የሆነ የስሜት መረበሽን ያስከትላል፡፡ እኔም በግሌ በኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ዙሪያ ጥናቴን ሳካሂድ በጣም ካሳዘኑኝ እና እጅግም ሰቀጠጡኝ ድርጊቶች ዋነኛው የግርፋቱ ሂደት ነው፡፡ ንጹሕ እና ፍጹም ከኃጢያት ነጻ የነበረው ክርስቶስ ያለበደሉ መገረፉ በራሱ አሳዛኝ ቢሆንም፤ በወቅቱ ሮማውያኑ ሰው የሚገርፉበትን ሁኔታ እጅቅ ከባድ፣ አሰቃቂ እና ርህራሄ የጎደለው ነበር – ይህ የግርፋት ሂደት በተለይም ከታሪክ መዛግብቶች እየተነበበ ውስጠ ነገሩ ደግሞ በሕክምናው ዐይን ሲመረመር ዘግናኝነቱ እጅግ ይጨምራል፡፡

ለመሆኑ በወቅቱ ሮማዊያን ሰዎችን የሚገርፉበት ሂደት ምን አይነት ነበር?

በግርፋት ሰዎችን መቅጣት በሮማውያን ዘንድ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ሕዝቦችና ስልጣኔዎች ውስጥ ይከወን ነበር፡፡ ሮማውያኑ ግን በአካባቢያቸው ይገኙ የነበሩ ባህሎችን እና ተግባራትን ወርሰው፤ በራሳቸው የሚጨመረውን ጨምረው እና የሚቀነሰውን በመቀነስ አሻሽለው የመጠቀም አዝማሚያ ስለነበራቸው – የግርፋት ስርዓታቸው በአካባቢው ከሚገኙ ሥልጣኔዎች ጋር ካለው ሂደት ስናነጻጽረው የተለየ ነበር፡፡ በዚህም ረገድ ግርፋት በሚገረፈው ሰው ላይ እጅግ ከባድ የሆነ ሕመም እና ስቃይ እንዲያስከትል ከመግረፊያ ጅራፋቸው አንስቶ እስከ አገራረፉ ሁኔታ ድረስ ማሻሻያ አድርገውበት ነበር፡፡ በወቅቱ በስቅላት እንዲሞቱ የሚፈረድባቸውን ሰዎች በአደባባይ ለማዋረድ፣ አልፎም ደግሞ በአካል ለማድከም በራሳቸው መንገድ ይገርፏቸው ነበር፤ ይባስ ብሎም በወቅቱ በስቅላት እንዲሞቱ የሚፈረድባቸው ሰዎች በቅድሚያ እንዲገረፉ የሚያስገድድ ሕግም ነበራቸው፡፡[4]

ሮማውያን ለግርፋት ከሚጠቀሙበት ጅራፍ እንጀምር፡፡ የሮማ ወታደሮች ለግርፋት የሚጠቀሙበት ጅራፍ በሚገረፈው ሰው ላይ ከፍተኛ ጉዳትን እንዲያስከትል ተደርጎ በጥንቃቄ እና በተጠና ሁኔታ የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህ ጅራፍ ከጠንካራ ቆዳ ተገምዶ የተሰራ ሲሆን በቆዳውም ላይ በተወሰኑ ሳንቲሜትሮች ርቀት ላይ ድቡልቡል የብረት ኳሶች አሉት፡፡ በተጨማሪም በመግረፊያ ጅራፉ ላይ በሚገኙት ቆዳዎች ጫፍ ላይ ከበግ አጥንት ወይንም ከብረት የተሰሩ እጅግ ሹል መውጊያዎች ነበሩት፡፡[5] ግርፋቱ በሁለት ወታደሮች ወይንም ቦታውን እየቀያየረ በሚገርፍ አንድ ወታደር ሊካሄድ ይችላል፡፡

3.1.1 አሰቃቂው የግርፋት ሂደት

ግርፋቱ ከመጀመሩ በፊት ለመግረፍ እንዲመች – አልፎም ደግሞ ተገራፊውን በአደባባይ ለማዋረድ ሲባል – የሚገረፈው ሰው ልብሱን እንዲገፈፍ ይደረግና ቀጥ ብሎ ከቆመ ወፍራም እንጨት ላይ እጁ በብረት ካቴና ይታሰራል፡፡[6] የግርፋቱ ሂደት ሲጀምርም፤ ገራፊው ወታደር [ወይም ወታደሮች] ጅራፉን በሙሉ ኃይላቸው በተገራፊ ጀርባ ላይ ያሳርፋሉ፡፡ ጅራፉ በተገራፊው ጀርባ ላይ በሚያርፍበት ጊዜ ከትከሻው እስከ መቀመጫው ድረስ ያገኘዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ሦስት አይነት ጉዳቶች በተገራፊው ላይ ይከሰታሉ፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ፣ ጅራፉ የተገመደበት ጠንካራ ቆዳ በተገራፊው ሰው ቆዳ ላይ ሲያርፍ ከፍተኛ ድምጽን ያሰማል – ከቆዳው ጋር በከፍተኛ ኃይል ስለሚገናኝም መበለዝ [Bruising] እንዲፈጥር ያደርጋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በቆዳው ውስጥ አብረው የተገመዱት የብረት ኳሶች የተገራፊውን ቆዳ ስለሚቀጠቅጡት ሰንበሮች[Contusions] እንዲፈጠሩ ያደርጋሉ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ከጅራፉ ጫፍ ላይ የሚታሰሩት ከበግ አጥንት ወይንም ደግሞ ከብረት የሚሰሩት ሹል ጫፎች በሚገረፈው ሰው ሥጋ ላይ በከፍተኛ ኃይል ይሰካሉ፤ በዚህም ጊዜ ውስጠኛው የቆዳ ክፍል [Subcutaneous tissue] ድረስ ተሰግስገው ይገባሉ፡፡[7] ገራፊው ወታደር ድጋሚ ለመግረፍ ጅራፉን ወደኋላ ሲስበውም፤ ይህ ከበግ አጥንት ወይንም ከብረት የሚሰራው ሹል ጫፍ የተሰገሰገበትን ቆዳ እና ሥጋ በመቦጨቅ ወደ መሬት ላይ ይበታትናል፡፡ በዚህ መልኩ ከቆዳው ግርፋት የሚፈጠረው መበለዝ [Bruising] ላይ ከተገመዱት የብረት ኳሶች የሚፈጠረው ሰንበር [Contusion] ሲደመርበት የተገራፊው ቆዳ መከፈት እና መተርተር ይጀምራል፡፡ የታሪክ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ በዚህ መልክ የሚገረፈው ሰው፤ በተወሰኑ ግርፋቶች ውስጥ ብቻ እጅግ ስለሚጎዳ ቆዳው ከእይታ ጠፍቶ ከቆዳው ሥር የሚገኘው ሥጋ ደም ለብሶ እንደሚታይ ያትታሉ፡፡[8] ይህ ጅራፍ የሚገረፈውን ሰው ከላይ ከትከሻው እስከ መቀመጫው ድረስ – አንዳንዴም አልፎ የኋላ እግሩን ክፍል ጭምር ስለሚያገኘው ከላይ እስከ ታች በሚባል ሁኔታ ሙሉ በሙሉ በደም የተሸፈነ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግርፋት እጅግ በጣም አሰቃቂ ከመሆኑ የተነሳ የሚገረፈው ሰው የጀርባ አጥንት [Spinal Cord] በግልጽ የሚታይበት ጊዜም ነበር፡፡[9]

ግርፋቱን የሚያከናውኑት ወታደሮቹ በአብዛኛው ግርፋቱን የሚያካሄዱት ከጎን በኩል ሆነው ስለሆነ፤ ቆዳ የሆነው የጅራፉ አካል በተገራፊው የጀርባ ቆዳ ላይ ሲያርፍ፤ ከብረት የተሰፉት ሹል ጫፎቹ ደግሞ ዞረው የተገራፊው ደረት ላይ ያርፉ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ በደረት ላይም ከፍተኛ የሆነ መበለዝ [Bruising] ስለሚፈጠር እና በደረቱ ያለው ያለው ቆዳ እና ሥጋ ተበታትኖ በመሬት ላይ ስለሚዘራ፤ የሚገረፈው ሰው ትንፋሽ ወደ ውስጥ በሚስብበት ወቅት ከፍተኛ የሆነ ስቃይ ውስጥ ይገባ ነበር፡፡[10] በአይሁድ ሕግ መሰረት ማንኛውም ግርፋቶች ከአርባ እንዳይበልጡ የተደነገገ ቢሆንም፤ ብዙ ጊዜ ግን የግርፋቱ መጠን የሚወሰነው በወታደሮቹ የግል ፍላጎት እና ብርታት ላይ ነበር፡፡[11] ከግርፋቱ አሰቃቂነት የተነሳ ብዙዎቹ ሰዎች ግርፋቱ ሳይጠናቀቅ የሚሞቱ ሲሆን፤ ከሕመምና ስቃይ ብዛት የተነሳ የሚያብዱም እንደነበሩ በታሪክ መዛግብቶች ላይ ሰፍሮ እናገኛለን፡፡ በግርፊያው ወቅት ሳይሞቱ ወይም በስቃይ ብዛት ሳያብዱ ተርፈው ሊሰቀሉ የሚያቀኑ ሰዎች እጅግ በጣም ጥቂት ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት ይህ የግርፋት ስርዓት “ግማሽ ሞት” የሚል መጠሪያን ያተረፈ ሲሆን፤ እንዲህ የተባለበትም ምክንያት ከግርፋት የተረፉ ሰዎች በሞት እና በሕይወት መካከል ስለሚሆኑ ነው፡፡ ይህንን መሳይ ሰቅጣጭ የግርፋት ስርዓት ሳይሞቱ ወይም በሕመም ብዛት ሳያብዱ የጨረሱ ሰዎች አንድም ከሚፈጠርባቸው ከባድ ሕመም፤ አንድም ደግሞ ከደም እጦት የተነሳ አቅም ስለሚያንሳቸው መቆም ያቅታቸዋል፡፡ ከትከሻ አንስቶ እስከ መቀመጫቸው፤ አልፎም ደግሞ ከደረታቸውም ጭምር የሚፈሰው ደምም ቦታውን ስለሚያጨቀየው፤ የሚገረፈው ሰው በሰውነቱ ውስጥ ካለው ደም ውስጥ አብዛኛው ፈስሶ ያልቃል፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተከሰተውም እንዲህ ያለው ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ያህል ጊዜ እንደተገረፈ የሚጠቅስ ቃል በወንጌሉ ውስጥ ባናገኝም፤ በሐዲስ ኪዳን ውስጥ ፍንጭ የሚሰጠን ክፍል አለ፡፡ የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ በቀዳሚት መልእክቱ ሲጽፍ ‹‹እስመ፡ በቊስለ፡ ዚአሁ፡ ሐየውክሙ፡ ቊስለክሙ – በእርሱ ቁስል የእናንተ ቁስል ተፈወሰ››[1 ጴጥ 2፡25] ብሎ ጽፏል፡፡ የተጻፈበትን የግሪክ ቋንቋ ስናነብ የተጠቀመው ቃል “ሞሎፒ” (μώλωπι) የሚል ሲሆን፤ ቃሉን እና የግሪኩን ሰዋስው አወቃቀር ስንመለከት ግርፋቱ እጅግ ከባድና አሰቃቂ እንደነበረ ፍንጭ ሰጪ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡[12]

3.1.2 ከግርፋቱ መጠናቀቅ በኋላ

በዚህ መልክ ተገራፊው ግርፋቱ ሲያበቃለት በሕመም ብዛት ካላበደ ወይንም ደግሞ በደም እጦት ምክንያት ሕይወቱ ካላለፈ፤ በሰውነቱ ውስጥ ያለው ደም በብዛት ፈስሶ ስለሚያልቅ፤ በሕክምናው አጠራር ሃይፖቮሌሚክ ሾክ [Hypovolemic Shock] የሚባለው በሰውነቱ ውስጥ ይከሰታል፡፡ ሃይፖቮሌሚክ ሾክ [Hypovolemic Shock] ማለት ሰው በሰውነቱ ውስጥ ካለው ደሞ አንድ አምስተኛውን [ሃያ በመቶ] የሚሆነውን ደሙን ሲያጣ ነው፡፡[13] የሚገረፈው ግለሰብ ሃይፖቮሌሚክ ሾክ [Hypovolemic Shock] በሚባለው ሁኔታ ሲገባ አራት ዋና ዋና ነገሮች ይከሰታሉ፡፡ በመጀመሪያ ተገራፊው ሰው ብዙ ደም በማጣቱ ምክንያት ልቡ በሰውነት ውስጥ የቀረውን ደም ለተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ለማዳረስ ሲል በከፍተኛ ፍጥነት መምታት ይጀምራል፡፡ ሁለተኛው በሰውነት ውስጥ ያለው የደም መጠን ስለሚቀንስ፤ የደም ግፊት አብሮ ይቀንስና – ራስ መሳት/ መውደቅን ያስከትላል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ በሰውነት ውስጥ ያለው ደም በብዛት ስለፈሰሰ እና ሰውነት ደግሞ አጠቃላይ የፈሳሽ መጠን ባለበት ለማቆየት የተቻለውን ማድረግ ስለሚኖርበት፤ የተገራፊው ኩላሊቶች ፈሳሽ በሽንት በኩል ወጥቶ ጭራሽ ሰውነት የፈሳሽ መጠኑ እንዳይቀንስ ለማድረግ ኩላሊቶች ፈሳሽ እንዲፈጠር ማድረጋቸውን ያቆማሉ፡፡ በአራተኛ ደረጃ ደግሞ በሰውነት ውስጥ ያለውን የፈሳሽ እጥረት በመኖሩ፤ ተገራፊው በከፍተኛ ሁኔታ የውሃ ጥም ያጋጥመዋል፡፡ [14]

3.1.3 የእሾህ አክሊሉ ሕማም

ቅዱስ ማቴዎስ የሮማውያኑን ግርፋት በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ሆኖ መቋቋም የቻለው ኢየሱስ ክርስቶስ የእሾህ አክሊል ማድረጉን ሲገልጽ “ጭፍሮች የእሾህ አክሊል ጎንጉነው በራሱ ላይ አቀዳጁት” [ማቴ 27፡29] በማለት ነው፡፡ ይህ የእሾህ አክሊል በብዙ ክርስቲያኖች ዘንድ ብዙም አጽንኦት ሳይሰጠው ቢታለፍም፤ የነበረው ሕማም ግን እጅግ ከባድ ነበር፡፡ የእሾህ አክሊሉ የተገኘው በሳይንሳዊ አጠራሩ ዚዚፐስ ስፒና ክሪስቲ [Zizipus Spina – Christi] ተብሎ ወይም በተለምዶ የሶሪያው የክርስቶስ እሾክ [Syrian Christ Thorn] ከሚባለው ተክል እንደሆነ የሮም ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡

ይህ ዚዚፐስ ስፒና ክሪስቲ [Zizipus Spina – Christi] የተባለው ተክል ላይ የሚገኙት እሾሆች እጅግ በጣም ጠንካራ ከመሆናቸው የተነሳ የሥነ-ተክል ተመራማሪዎች ጥንካሬያቸው ለመግለጽ “እንደሚስማር የጠነከሩ” እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ሮማውያን ወታደሮችም ከዚህ ተክል የተወሰደውን እሾህ በጉንጉን መልክ አድርገው በጭንቅላቱ ላይ ሲያስቀምጡ በሃይል በመግፋታቸው፤ በሚያስቀምጡበት ጊዜ በክርስቶስ ፊቱ ዙሪያ የሚገኙትን ትራይጄሚናል ነርቮች [Trigeminal Nerves] ተብለው የሚታወቁትን ነርቮችን ወግተዋቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተከሰተው፤ በሕክምናው ቋንቋ ትራይጄሚናል ኒውራልጂያ [Trigeminal Neuralgia] የምንለው ሲሆን የሚከሰተውም ትራይጄሚናል ነርቮች [Trigeminal Nerves] ላይ ጉዳት ሲደርስ ነው፡፡ ሕመሙም በሁሉም የፊቱ አቅጣጫዎች እና በጆሮው የውስጠኛ ክፍል ጭምር በኩል በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሰማው ያደርጋል፡፡ ይህ ትራይጄሚናል ኒውራልጂያ [Trigeminal Neuralgia] በሚከሰትበት ጊዜ ያለው ሕመም እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ፤ በአሁኑ ሰዓት በዚህ ሕመም የተጠቁ ሰዎች ሕመሙን ሲገልጹት “ፊትን ሁሉ በሳለ ቢላዋ ወይም በብዙ መርፌዎች የመወጋት ያህል ይሰማል” በማለት ነው፡፡

3.1.4 የጎልጎታው ረጅም ጉዞ

የግርፋቱን ሂደት ተቋቁሞ በሕይወት የተረፈ ሰው፤ እርሱ ራሱ የሚሰቀልበትን መስቀል ተሸክሞ እስከመሰቀያው ቦታ ድረስ ይወጣ ነበር፡፡ ከአሰቃቂው ግርፋቱ በኋላ የሚኖሩውን ሁኔታ በዝርዝር ከላይ ስለገለጽኩት፤ የሚገረፈው ሰው በአቅም እጦት መቆም እንኳን በማይችልበት ሁኔታ ላይ ሆኖ መስቀልን የሚያክል ከባድ ነገር አሸክሞ ዳገታማ ተራራ እንዲወጣ ማድረግ የሚኖረውን ክብደት እና ስቃይ እንድታስቡት ለእናንተው እተወዋለሁ፡፡

በሮማውያን ዘንድ አንድ ሰው የሚሰቀልበት መስቀል ሙሉ ክብደቱ ከ 136 ኪሎግራም በላይ ይመዝን ስለነበር፤ የሚሰቀለውን ሰው የሚያሸክሙት ሲሰቀል እጁ የሚያርፍበትን እና በሙያዊ አጠራሩ ፓቲቡለም [Patibulum] ተብሎ የሚጠራውን የመስቀሉን ክፍል ነበር፡፡ ይህም ፓቲቡለም [Patibulum] እጅግ ግዙፍ ስለነበረ፤ ብቻውን ከ 36 ኪሎግራም እስከ 57 ኪሎግራም ድረስ ይመዝን ነበር፡፡[15] እንኳን በሮማውያን አሰቃቂ ግርፋት ውስጥ ያለፈ ሰው ይቅርና፤ በሙሉ ጤንነት ላይ የሚገኝ ሰው እንኳን ሳይቀር ከ 36 ኪሎግራም እስከ 57 ኪሎግራም ድረስ የሚመዝን የመስቀል አግድም እንጨት ተሸክሞ ዳገት የሆነን ተራራ መውጣት ምን ያህል ሊከብድ እንደሚችል መገመት አያቅተንም፡፡ አስቀድመን እንዳየነው ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውነቱ ውስጥ ካለው ደም ብዙውን ስላጣ ሃይፖቮሌሚክ ሾክ [Hypovolemic Shock] ላይ ስለነበረ፤ በወንጌሉ ስንመለከት መስቀሉን መሸከም እጅግ ከብዶት በተደጋጋሚ ይወድቅ እንደነበር እና ሮማውያኑም እንዲህ መሆኑን ተመልክተው ስምዖን መስቀሉን እንዲሸከምለት ያደረጉበት አስገዳጅ ሁኔታ መፈጠሩን እናነባለን፡፡

❹ ስቅላት

4.1 የስቅላት ቅጣት ቅድመ ታሪክ

በታሪክ መዛግብቶች መሰረት፤ ሰዎችን በስቅላት መቅጣት የተጀመረው በፋርስ [ኢራን] እንደሆነ ይታመናል፡፡[16] በወቅቱ የፋርስ ሰዎች የሚያመልኩት ኦር-ማሕዜድ የተባለው ጣዖት ‹ምድርን ቀድሷታል› ብለው ያስቡ ስለነበር፤ የሚቀጧቸውን ሰዎች ምድርን እንዳያረክሱ በማለት ከመሬት ከፍ አድርገው ይሰቅሏቸው ነበር፡፡ ታላቁ አሌክሳንደርም ግዛቱን በሚያስፋፋበት ወቅት፤ በስቅላት የመቅጣት መንገድን በግብጽ እና በካርቴጅ እንዲታወቅ አድርጎታል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሰቀሉት ሮማውያንም ደግሞ ስቅላትን ከካርቴጅ ሕዝቦች ሊማሩ ችለዋል፡፡ ሆኖም ግን፤ ሮማውያን በካርቴጅ ሕዝቦች ዘንድ ያዩትን የስቅላት መንገድ በራሳቸው በማሻሻል – በሚሰቀለው ሰው ላይ ከፍተኛ ሕመምን እና አሰቃቂ ሞትን እንዲያስከትል አድርገውታል፡፡ በስቅላት ሰዎችን መቅጣት እጅግ አሰቃቂ መሆኑን ራሳቸው ሮማውያን ይረዱት ስለነበረ፤ በዚህ መንገድ እንዲሞቱ የሚፈረድባቸው ከፍተኛ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች፣ ከአሳዳሪዎቻቸው አምልጠው የጠፉ አገልጋዮች እና በሮማውያን እጅ የወደቁ ጠላቶች ነበሩ፡፡ በሮም ሕግ መሰረት ማንኛውም ሮማዊ በስቅላት የማይቀጣ ሲሆን፤ ሮማዊ የሆነ ሰው በስቅላት የሚቀጣው ወታደር ሆኖ ‹በሀገር ክህደት› ከተወነጀለ ብቻ ነበር፡፡

4.2 የስቅላት ሂደት

እርሱ ራሱ የሚሰቀልበትን መስቀል አግዳሚ ተሸክሞ የሚሰቀልበት ቦታ ላይ የደረሰው ሰው፤ ተሸክሞት በመጣው የመስቀሉ አግድም ክፍል ቀጥ ካለ ትልቅ እንጨት ጋር እንዲጣበቅ ይደረጋል፡፡ ከዚያ በመቀጠል፣ የሚሰቀለው ሰው ተሸክሞት ከመጣው አግዳሚ እንጨት ጋር በሚስማር ተመትቶ እንዲያያዝ ይደረጋል፡፡ ሮማውያን ወታደሮች የሚሰቀለውን ሰው ከእንጨቱ የሚያያይዙት ከ 13 ሴንቲሜትር እስከ 18 ሴንቲሜትር ርዝመት ባለው የብረት ሚስማር ነበር፡፡ ይህ ሚስማር በሚሰቀለው ሰው የእጅ አንጓ ላይ ይመታል፡፡ በዚህ ጊዜም ሚስማሩ ብራኪያል ፕሬክሲስ [Brachial Prexis] ከሚባለው የነርቭ ስብስብ ከሚወጡት አምስት ዋና ዋና ነርቮች አንደኛው የሆነውን ሜዲያን ነርቭ [Median Nerve] ሰንጥቆት ያልፋል፡፡ ይህ ሲሆን ያለውን ሕመም ለመግለጽ እጅግ ከባድ ነው፡፡ አንድ የሕክምና ዶክተር ይህንን ሲገልጹ “ከክርናችሁ ጫፍ ላይ ወንበር ወይም የጠረጴዛ ጠርዝ መትቷችሁ የሚያውቅ ከሆነ ከፍተኛ ንዝረት እና ሕመም ይሰማችኋል፡፡ ሚስማሩ ሰንጥቆ የሚያልፈው ይህንን ነርቭ ነው፤ በዚህ ጊዜ የሚኖረውን ሕመም ለመረዳት ከፈለጋቸው ወንበር ሲመታችሁ በብርቱ የሚያሰማችሁን ነርቭ አንድ ሰው በመቆንጠጫ እየጠመዘዘ ቢያወጣው ሊሰማችሁ ከሚችለው ሕመም ጋር ሊወዳደር ይችላል” በማለት ገልጸውታል፡፡

ይህ በስቅላት ሰዎችን በሞት የመቅጣት ሂደት እጅግ ዘግናኝ እና ከፍተኛ ሥቃይ የተሞላበት ከመሆኑ የተነሳ፤ የተሰቀለ ሰው የሚያልፍበትን ሕመም የሚገልጽ ቃል ባለመገኘቱ ኤክስክሩሺዬቲንግ [Excruciating] የሚል አዲስ ቃል ሊፈጠርለት ግድ ብሏል፡፡[17] የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእጁ አንጓ ላይ በሚስማር ሲቸነከር ያለውን አይነት ከባድ እና አሰቃቂ ሕመም፤ ሚስማሩ እግሩ ላይ ሲቸነከርም በድጋሚ ይከሰታል፡፡ ሮማውያን ወታደሮች በዚህ አይነት መንገድ ተሰቃዩን ሰው ከአግዳሚ እንጨቱ ጋር ካያያዙት በኋላ፤ መስቀሉን በገመድ አድርገው ከመሬት በመጎተት ቀጥ አድርገው እንዲቆም ያደርጉታል፡፡

“ጸሎተ ሐሙስ፡ ከሥነ-ልቦና ሳይንስ እይታ” በተሰኘው ጽሑፌ ላይ እንደዳሰስኩት፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ከጸሎተ ሐሙስ ጀምሮ ከፍተኛ ጭንቀት [Severe Stress]፣ የእንቅልፍ እጦት[Acute Sleep Deprivation]፣ ከፍተኛ ድካም[Fatigue]፣ አንድ ላይ በመሆን እጅግ ጎድተውት ነበር፡፡ ይሄም ደግሞ ከነበሩት ሁኔታዎች እና ከቅዱስ ሉቃስ የግሪክ ቃል አጠቃቀም ተነስተው የሕክምና ሊቃውንት ሄማቲድሮሲስ[Hematidrosis] ብለው የሚጠሩት የደም ወዝ መከሰቱን ይናገራሉ፡፡ ይህንን ሃሳብ ከተቀበልንም፤ ከመገረፉ በፊት ቆዳው እጅግ እንዲሳሳ አድርጎታል – በዚህም ምክንያት ደግሞ በአሰቃቂው የሮማውያን ግርፋት ወቅት ያለውን ሕመሙን ከልክ በላይ ጨምሮታል ማለት ነው፡፡ በተጨማሪ አይሁድ ከያዙት በኃላ ከአንዱ ወደ አንዱ ቦታ ሲጓዝ በአማካኝ ወደ 4 ኪሎሜትር በላይ መንገድ በእግሩ እንደተንከራተተ አይተናል፡፡ ብዙዎች የማይወጡትን የሮማውያን ግርፋት ካለፈም በኋላ ሃይፖቮሌሚክ ሾክ [Hypovolemic Shock] በሚባለው ሁኔታ ላይ እንደነበረ እና በዚህም ምክንያት እጅግ በመዳከሙ መቆም ጭምር የማይችልበት ሁኔታ ላይ እንደነበረ አይተናል፡፡ እንዲህ “በሞትና በሕይወት” መካከል በሚባል ሁኔታ ላይ እያለም፤ ስምዖን እስኪቀበለው ድረስ ከ 35 ኪሎግራም እስከ 57 ኪሎግራም ድረስ የሚመዝነውን የመስቀል አግዳሚ እንጨት ወደ ጎልጎታ በዳገት ላይ ተሸክሞ እንደተጓዘ፤ አቅም በማጣቱም በተደጋጋሚ ይወድቅ እንደነበር አይተናል፡፡ ከዚህም በኋላ ከ 13 ሳንቲሜትር እስከ 18 ሳንቲሜትር ርዝመት ባለው የብረት ሚስማር እጅ እና እግሩን እንደተቸነከረ፤ ይሄም ደግሞ ሜዲያን ነርቭ [Median Nerve] ተብሎ የሚጠራውን ነርቭ ሰንጥቆ በማለፉ ምክንያት እጅግ አሰቃቂ ሕመምን እንደተቀበለ አይተናል፡፡

4.3 የመስቀል ላይ ቆይታ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎም ያሳለፈውን ሕመም ደግሞ በዚህ ንዑስ ክፍል እንመለከታለን፡፡ አንድ ሰው በመስቀል ላይ ሲሰቀል፤ ሙሉ ሰውነቱ ወደፊት ስለሚያዘነብል እና እጆቹም መቋቋም ስለማይችሉ በሁለቱም እጆቹ ላይ ውልቃት [Dislocation] ያጋጥመዋል፡፡ ሁለቱም እጆቹ ከትከሻው ተለያይተው ወልቀው ሳለ በዚያ ሁኔታ ረግቶ መቆየት እጅግ ከባድ ሕመም አለው፡፡ በተጨማሪም ወደፊት ማዘንበሉ ከፍተኛ ጫና በሳንባዎች ላይ ስለሚያሳድር፣ በግርፋቱ ጊዜ በደረቱ ላይ ከደረሰው ከፍተኛ ጉዳት ጋር ተዳምሮ ለመተንፈስ ከመቼውም ጊዜ በላይ እጅግ ስቃይ የተሞላበት ይሆናል፡፡ የተሰቀለው ሰው ለመተንፈስ ያለው ብቸኛ አማራጭ፤ በእግሩ በመደገፍና ሰውነቱን ወደላይ በመግፋት እና ቀና በማድረግ አየር ይስባል፡፡ በግርፋት ምክንያት “በሞትና በሕይወት መካከል” ለሆነ ሰው አንድ ጊዜ እንኳን ራስን በእግር ኃይል ከፍ አድርጎ አየር መሳብ ምን ያህል ጣር ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡

ይህን በሚያደርግበት ጊዜ የእግሩ ሁለተኛ እና ሦስተኛ አነስተኛ አጥንቶች፤ ወይም በሕክምናው መጠሪያ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ሜታታርሳል [2nd and 3rd Metatarsals] ተብለው በሚታወቁት የእግር አነስተኛ አጥንቶች መካከል አልፎ የተቸነከረው ሚስማር ስለሚነቃነቅ ከፍተኛ ሕመም እንዲሰማው ያደርጋል፡፡ ራ

ሱን በእግሩ ኃይል ወደላይ ሲገፋም ጀርባው ከመስቀሉ እንጨት ጋር ስለሚፋፋቅ እና ቁስሎች ስለሚፍቃቸው ሕመሙ እጥፍ ድርብ ይሆናል፡፡ የተሰቀለው ሰው እጅግ ስለሚደክም ከተወሰነ ጊዜ በኃላ ራሱን ከእግሩ ገፍቶ እና ከፍ ብሎ አየር ለመሳብ የሚችልበት አቅም ያጣል፡፡ አቅም ቢኖረው እንኳን ለረጅም ጊዜ መጠበቅ የማይፈልጉት የሮም ወታደሮች እራሱን ከእግሩ ከፍ አድርጎ አየር መሳብ እንዳይችሉ የሰዎችን ጭን ይሰብሩ ስለነበር [ዮሐ 19፡32] በመስቀል ላይ ያለው ሰው ትንፋሽ እያጠረው ቀስ ያለና ስቃይ የሞላበት ሞት እንዲሞት ያደረግ ነበር፡፡
በስቅላቱ ወቅት በሳንባ ላይ የሚፈጠረው ጫና
የተሰቀለው ሰው ከፍ ብሎ አየር መሳብ እያቃተው ሲመጣ፤ በሕክምናው አጠራር ሪስፓራቶሪ አሲዶሲስ [Respiratory Acidosis] የሚባለው ይከሰታል፡፡ በዚህም ጊዜ የተሰቀለው ሰው ደም ውስጥ የሚገኘው ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደ ካርቦኒክ አሲድ ስለሚለወጥ በደም ውስጥ ያለው የአሲድ መጠን ከፍ ይላል፡፡ ይህም ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ የልብ ምት እንዲጨምር ያደርጋል – በዚህም ጊዜ የተሰቀለው ሰው ወደሞት እንደቀረበ ግልጽ ይሆንለታል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም ወደ ሞት መቅረቡን ባወቀ ጊዜ “ወጸርሐ፡ እግዚእ፡ ኢየሱስ፡ በዓቢይ፡ ቃል፡ ወይቤ፡ አባ፡ አመሐዕን፡ ነፍስየ፡ ውስተ፡ እዴከ – ያንጊዜም ጌታችን ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አደርጎ “አባት ሆይ ነፍሴን በአንተ እጅ አደራ እሰጣለሁ” ብሎ ጮኸ” [ሉቃ 23፡46] በማለት ይገልጸዋል፡፡ በመስቀል ላይ በዚህ ዓይነት አሰቃቂ መንገድ ሕይወቱ አልፏል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ በግርፋቱ ጊዜ ከፍተኛ ደም ስለፈሰሰው ሃይፖቮሌሚክ ሾክ [Hypovolemic Shock] ውስጥ መግባቱን አስቀድመን አይተናል፡፡ በዚህ ሃይፖቮሌሚክ ሾክ [Hypovolemic Shock] ሆኖ ሳለ በሕክምናው አጠራር በልቡ ዙሪያ ፔሪካርዲያል ኢፊውዥን [Pericardial Effusion] መፈጠሩ አይቀርም – ይህም ደግሞ ማለት በልብ ዙሪያ የሚኖር የፈሳሽ ጥርቅምን ያመለክታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፕሌውራል ኤፊውዥን [Pleural Effusion] በመባል የሚታወቀውም ይከሰታል – ይህ ደግሞ በደረት አካባቢ የሚኖርን የፈሳሽ ክምችት ይጠቁማል፡፡ የዚህንም ማረጋገጫ በወንጌሉ እናገኛለን፡፡ በመስቀል ላይ ከሞተ በኃላ አንድ የሮም ወታደር መጥቶ ጎኑን ሲወጋው ደም እና ውኃ እንደወጣ [ዮሐ 19፡34] ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ይህም ደግሞ እስካሁን ድረስ ካየነው የሕክምና መረጃ ጋር የሚጣጣም ሲሆን – ከጎኑ ደም እና ውሃ ተቀላቅሎ መውጠቱም በመስቀል ላይ እንደሞተ ማረጋገጫው ነው፡፡[18]
✢ ማጠቃለያ
የክርስቶስን ሕማም ከብዙ በጥቂቱ በሕክምና ሳይንስ መነጽርነት እና አምላክ በፈቀደልን ልክ ለማየት ሞክረናል፡፡ ከሁሉም በላይ የክርስቶስን ሕማም ስናስብ – ከላይ ከሕክምና መረጃ ጋር አድርገን የተመለከትነው የጌታችን ሕማም ስናሰላስልም – የተከፈለልን ዋጋ እስከምን ድረስ እንደሆነ የሚያስታውሰን ነው፡፡ በሕይወታችንም ትልቁ ነጥብ መሆን ያለበት የተከፈለልንን ዋጋ አውቀን እያንዳንዱን የሕይወታችንን ቅጽበት ክርስቶስን በመውደድ፣ እርሱ የከፈለልንን መስዋእት እያሰቡ ሕይወታችንን በትህትና በመኖር እና እለት ከእለት ክርስቶስን በመምሰል ሒደት ውስጥ መንፈሳዊ ደረጃችንን እያሳደግን መሄድ መሆን አለበት፡፡ ሕመሙ በአእምሯችን እና በልባችን ውስጥ ቦታ እንዲኖረው ቅዱስ አምላካችን እግዚአብሔር ሁላችንን ይርዳን፡፡
➻ Fresenbet G.Y Adhanom
° ማጣቀሻ ጽሑፎች [APA ሥልት የተከተለ] °
[1] – ሄኖክ ኃይሌ(2010)፣ ሕማማት፣ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ፣ ማዕረግ ማተሚያ፣ ገጽ 37.
[2] – ሊቃውንተ ኢትዮጵያ(1988)፣ ወንጌል ቅዱስ፡ ዘዜነወ ማቴዎስ፡ ወማርቆስ ሉቃስ፡ ወዮሐንስ፣ ተስፋ ገብረ ሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ፣ ገጽ 593.
[3] – William D. Edwards, MD; Wesley J. Gabel, Mdiv; Floyd E. Hosmer, MS, AMI (1986). On the Physical Death of Jesus Christ. JAMA 255:1455-1463.
[4] – Hengel M (1977), Bowden J (trans). Crucifixion in the Ancient World and the Folly of the Message of the Cross. Philadelphia. Fortress Press. Pp 22-45, 86-90.
[5] – Bucklin R (1970). The Legal and Medical Aspects of the Trial and Death of Christ. Sci Law. 10:14-26.
[6] – Barbet P. Earl of Wicklow (trans.) (1953). A Doctor at Calvary: The Passion of Our Lord Jesus Christ as Described by a Surgeon. Garden City, NY. Doubleday Image Books. pp 12-18, 159-175.
[7] – Davis CT (1965). The Crucifixion of Jesus: The Passion of Christ from a Medical point of View. Ariz Med. 22:183-187.
[8] – Lee Strobel (1998). The Case for Christ: A Journalist’s Personal Investigation of the Evidence for Jesus. Grand Rapids, Michigan. Zondervan Publishing House. pp. 179.
[9] – Ibid.
[10] – Ibid.
[11] – Bucklin R (1970). The Legal and Medical Aspects of the Trial and Death of Christ. Sci Law. 10:14-26.
[12] – Wuest KS (1973). Wuest Word Studies From the Greek New Testament for the English Reader. Grand Rapids, Mich. WB Eerdmans Publisher. Vol 1. pp. 280.
[13] – Lee Strobel (1998). The Case for Christ: A Journalist’s Personal Investigation of the Evidence for Jesus. Grand Rapids, Michigan. Zondervan Publishing House. pp. 179.
[14] – Ibid.
[15] – Pfeiffer CF, Vos HF, Rea J(eds) (1975). Wycliffe Bible Encyclopedia. Chicago. Moody Press. Pp. 149-152, 404-405, 1173-1174.
[16] – Friedrich G. Bremiley G (ed-trans) (1971). Theological Dictionary of the New Testament. Grand Rapids, Mich. WB Eerdmans Publisher. Vol 7. pp. 572, 573, 632.
[17] – Lee Strobel (1998). The Case for Christ: A Journalist’s Personal Investigation of the Evidence for Jesus. Grand Rapids, Michigan. Zondervan Publishing House. pp. 181.
[18] – Davis CT (1965). The Crucifixion of Jesus: The Passion of Christ from a Medical point of View. Ariz Med. 22:183-187.

  • Images used from William D. Edwards, MD; Wesley J. Gabel, Mdiv; Floyd E. Hosmer, MS, AMI (1986). On the Physical Death of Jesus Christ. JAMA 255:1455-1463.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *