Heard Passion Week – Tuesday

ሠሉስ(ማክሰኞ)

የሰሙነ ህማማት ሠሉስ(ማክሰኞ) “የጥያቄ ቀን” በመባል ይታወቃል ምክንያቱም ሹመትን ወይም ስልጣንን ለሰው ልጅ የሰጠ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰኞ ባደረገው አንጾሖተ ቤተ መቅደስ ምክንያት በዚህ ዕለት ስለ ሥልጣኑ በጸሐፍት ፈሪሳውያን ተጠይቋልና ጥያቄውም ከምድራውያን ነገሥታት፣ ከሌዋውያን ካህናት ያይደለህ ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታት በማን ስልጣን ታደርጋለህ? የሚል ነበረ።

ይህንስ ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ እነግራችኃለው የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይ ወይስ ከሰው? አላቸው እነርሱም ከሰማይ ነው ብንል ለምን አልተቀበላችሁትም? ይለናል ከሰው ነው ብንል ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስን እንደ አባት ያከብሩታል እንደ መምህርም ይፈሩታልና ሕዝቡን እንፈራለን ተባብለው ወዴት እንደሆነ አናውቅም ብለው መለሱለት እርሱም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ እኔም አልነግራችሁም አላቸው ይህንንም መጠየቃቸው እርሱ የሚያደርጋቸው ሁሉ በራሱ ስልጣን እንዲያደርግ አጥተውት አልነበረም ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለተሞላ ነው እንጂ

ከዚህ የምንማረው የእነሱን ክፉ ጠባይና ግብር መከተል እንደማይገባን ነው በዚህ ዕለት በቤተ መቅደስም ረጅም ትምህርት ስላስተማረ የትምህርት ቀንም ይባላል ይኸውም ከሃይማኖት የራቁትን፣ ከፍቅረ እግዚአብሔር የተለዩትን አስተምሮ ማቅረብ፣ መክሮ መመለስ እንደሚገባ ሲያስተምረን ነው።

በማቴዎስ ወንጌል ፳፩፥፳፰፤ ፳፭፥፵፮፤ ማርቆስ ወንጌል ፲፪፥፲፪፤ ፲፫፥፴፯፤ በሉቃስ ወንጌል ፳፥፱፤ ፳፩፥፴፰ የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ማክሰኞ ዕለት የሚነገሩ ትምህርቶችን ይዘዋል፡፡ በዚህ ዕለት ጌታችን በቤተ መቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረ ዕለቱ የትምህርት ቀን ይባላል፡፡ ክርስቲያን የኾነ ዅሉ ከሥጋዊ ነገር ርቆ በዚህ ሰሞን የሃይማኖት ትምህርት ሲማር፣ ሲጠይቅ መሰንበቱ መጽሐፋዊ ሥርዓት ነው፡፡

በዚህ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሥልጣኑ ተጠይቋል፡፡ ጠያቂዎቹ የካህናት አለቆችና የሕዝብ አለቆች ሲኾኑ፣ ጥያቄውም፡- ‹‹በማን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህይህንስ ሥልጣን የሰጠህ ማነው?›› የሚል ነበር፡፡ ይህ ጥያቄ ጌታችን ሰኞ ዕለት ሁለት ነገሮችን ማከናወኑን ተከትሎ የተነሣ ጥያቄ ነው፡፡ ይኸውም ጌታችን ሲያደርጋቸው የነበሩ ተአምራትና ድንቅ ድንቅ ሥራዎች የካህናት አለቆችን ስላስቀኗቸው ጌታችንን ከሮማ መንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር ለማጋጨት የቀየሱት ስልት ነው፡፡ ጌታችን በቤተ መቅደስ የነበሩትን ነጋዴዎችን አባሯል፤ መደባቸውን ገለባብጧል፡፡ ነጋዴን ማባረርና መደብን ማስለቀቅ መንግሥታዊ ሥራ ነው፡፡ ጌታችን ‹‹በራሴ ሥልጣን›› ቢላቸው ፀረ መንግሥት አቋም አለው በማለት ከሮማ መንግሥት ዘንድ ለማሳጣት ነበር ዕቅዳቸው፡፡

ጌታችን ግን የፈሪሳውያንን ጠማማ አሳብ ስለሚያውቅ ‹‹የዮሐንስ ጥምቀት ከየት ነው? ከሰማይ ነው ወይስ ከምድር?›› ሲል ጠይቋቸዋል፡፡ ጌታችን ፈሪሳውያን ላቀረቡለት ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጠም፡፡ ምክንያቱም ጥያቄው ለከሳሾቹ ዓላማ መሳካት አመቺ ኹኔታን ስለሚፈጥር ጥያቄውን በጥያቄ መልሶላቸዋል፡፡ እነርሱም ‹‹ከሰማይ ነው›› ቢሉት ‹‹ለምን አላመናችሁበትም?›› እንዳይላቸው፤ ‹‹ከሰው ነው›› ቢሉት ደግሞ ሕዝቡ ዮሐንስን እንደ አባት ይፈሩት፣ እንደ መምህር ያከብሩት ነበርና ሕዝቡ እንዳይጣሏቸው ስለፈሩ ‹‹ከወዴት እንደ ኾነ አናውቅም›› ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም ‹‹እኔም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ አልነግራችሁም›› አላቸው፡፡ ይህን ጥያቄ መጠየቃቸውም እርሱ የሚያደርጋቸውን ተግባራት ዅሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተውት አልነበረም፤ ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለተሞላ ነበር እንጂ፡፡

ዛሬም ቢኾን መልካም ሥራን በሠራን ጊዜ ከልዩ ልዩ ወገኖች የሚመጡ ፈተናዎች ለመልካም ሥራችን እንቅፋት ሊኾኑ እንደሚችሉ መገንዘብ አለብን፡፡ ብዙ ወገኖች ‹‹ለቅን አሳባችን ለምን ሰዎች ክፉ ነገር ይመልሱልናል?›› በማለት ሲጠይቁ ይሰማል፡፡ ለቅን አሳባችን ከዓለም ዘንድ ተቃራኒ ነገር እንደሚጠብቀን ለመረዳት ‹‹ዓለም የሚወደው የገዛ ወገኑን ነው›› የሚለውን የጌታችንን ትምህርት ልብ ይሏል፡፡ በዘመናችን አሳልፈው ሊሰጡን የሚፈልጉ ሰዎች ፈታኝ ጥያቄ እንደሚያቀርቡልንም ከወዲሁ ልንገነዘብ ይገባል፡፡

እምበለ ደዌ ወሕማም፤

እምበለ ጻማ ወድካም አመ ከመ ዮመ ያብጸሐነ፤

ያብጸሐክሙ እግዚአብሔር በሰላም።

What Happened to Jesus on Holy Tuesday?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *