Heard Passion Week – Wednesday

እለተ ረቡዕ /እሮብ/ – ምክረ አይሁድ ይባላል

የአይሁድ ሊቃነ ካህናት ፀሀፍት ጌታችን እንደት መያዝ እንዳለባቸው ምክር ያጠናቀቁበት ቀን ነው። ማቴ 26÷3–5

የመልካም መአዛ ቀን ይባላል፦

ጌታችን በዚህ እለት በቤተ ስሞኦን ዘለምፆ ተቀምጦ ሳለ ማርያም ባንተፍረት/ባለሽቶዋ ማርያም/በአልባስጥሮስ ብልቃጥ የተሞላ ሽቶ ይዛ በመሄድ በፀጉሩ በራሱ ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባችው ነው። የእንባ ቀን ይባላል ፦

ማርያም ባአንተ እፍረት በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ መላ ሀጢአትዋን ይቅር እንድላት በእንባዋ እግሩን አጥባዋለችና በጠጉራም በእንባዋ ያጠበችውን እግሩን አብሰዋለችና። ማቴ 26÷6–7

በዚህ ቀን አስቆረቱ ይሁዳ ወደ ካህን አለቆች ሄዶ በ30 ብር ጌታችንን ሲሰጣቸው መስማማቱ በዚህ ቀን ይታሰባል።

#ረቡዕ እለት የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የመከሩበትና ውሳኔ ያሳለፉበት ቀን በመሆኑ ምክረ አይሁድ ይባላል። ወቅቱ የፋሲካን በዓል የሚያከብሩበት ቀን በመሆኑ እና ብዙ ህዝብም ጌታን ይከተለው ስለነበር ሁከት እንዳይነሳ ስጋት ነበራቸው ። ነገር ግን ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ስለነገራቸው ሉቃ ፳፪፥፩-፮ ጭንቀታቸው ተወግዶ በጌታ መያዝ ተስማምተዋል።

የመልካም መዓዛ ቀንም ይባላል፡
ጌታችን በዚህ ዕለት በለምጻሙ በሰምዖን ቤት ተቀምጦ ሳለ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት/ባለሽቶዋ ማርያም/ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ የአልባጥሮስ ሽቱ አምጥታ በራሱ ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባቸው ማቴ ፳፮፥፮-፯ የመዓዛ ቀን ይባላል።

የእንባ ቀን ይባላል፡-
ባለሽቱዋ ሴት (ማርያም እንተ እፍረት) ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት እየለመነች በእግሩ ስር ተደፍታ በእንባዋ እግሩን አርሳለችና ማር ፲፬፥፱ የእንባ ቀን ይባላል።

በቅዱስ ማቴዎስና በቅዱስ ማርቆስ አመዘጋገብ መሠረት በዕለተ ረቡዕ የሚከተሉት ሦስት ነገሮች ተፈጽመዋል፤

  • አንደኛ የካህናት አለቆች፣ የሕዝብ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ፈሪሳውያን በጌታችን ላይ  ተማክረዋል፤
  • ሁለተኛ ጌታችን በስምዖን ዘለምጽ ቤት ሳለ አንዲት የተጸጸተች ሴት ሽቱ ቀብታዋለች፡፡
  • ሦስተኛ ከዳተኛው ይሁዳ ጌታችንን አሳልፎ ለመስጠት ከጸሐፍት ፈሪሳውያንና ከካህናት አለቆች ዘንድ ሠላሳ ብር ለመቀበል ተስማምቷል፡፡

የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሹማምት በጌታችን ላይ ይሙት በቃ ለመወሰን የሰበሰቡት ሸንጐ ሲኒሃ ድርየም› ይባላል፡፡ በዚህ ሸንጐ ላይ በአብዛኛው የተሰየሙት ሰዱቃውያን ሲኾኑ ሌሎቹ ደግሞ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ነበሩ፡፡ ሸንጐው በአጠቃላይ ሰባ ሁለት አባላት የነበሩት ሲኾን የሚመራውም በሊቀ ካህናቱ በቀያፋ ነበር፡፡ በዕለቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት ይዘው እንደሚገድሉት አይሁድ በዚህ ሸንጎ መክረዋል፡፡ ከዳተኛው ይሁዳም ጸሐፍት ፈሪሳውያንና የካህናት አለቆች በጌታን ላይ የነበራቸውን ጥላቻ ያውቅ ስለነበር ‹‹ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ? እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤›› በማለት ጌታችን አሳልፎ ሊሰጣቸው እንደሚችል ተስማቷል፡፡

ጌታችን ያስተምር በነበረበት ወቅት የአስቆሮቱ ይሁዳ ከምእመናን ለሚገባው ገንዘብ ሰብሳቢ (ዐቃቤ ንዋይ) ነበር፡፡ ከሚሰበሰበው ሙዳየ ምጽዋት ለግል ጥቅሙ እየቀረጠ የማስቀረት የእጅ አመል ነበረበት፡፡ ይሁዳ ፍቅረ ንዋይ እንደሚያጠቃው ድብቅ አመሉ ጎልቶ የወጣው ጌታችን በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው ውድ የኾነ ሽቱ በቀባችው ጊዜ ነው፡፡ በዚያች ዕለት ይሁዳ የተቃውሞ ድምፅ ካሰሙት አንዱ ነበር፡፡

‹‹ይህ ሽቱ ተሽጦ ለድሆች ቢሰጥ መልካም ነበር፤›› በማለት ያቀረበው አሳብ ‹‹አዛኝ መሳይ ቅቤ አንጓች›› እንደሚባለው ነበር፡፡ ሽቱ ሲሸጥ የሚያገኘው ጥቅም አለ፤ ሽቶው በጌታችን እግር ሥር ከፈሰሰ ለእርሱ የሚተርፈው የለም፡፡ ይሁዳ ተቆርቋሪ መስሎ ያቀረበው አሳብ ተቀባይነት በማጣቱም ማኩረፊያ ያገኘ መስሎት በቀጥታ ከካህናት አለቆች ዘንድ ሔዶ ጌታንን በሠላሳ ብር ለመሸጥ ተዋዋለ፡፡ ይህ ታሪክም በሦስቱ ወንጌላት ውስጥ በሚከተሉት ምዕራፎች ተመዝግቦ እናገኛዋለን፤ ማቴ. ፳፮፥፫-፲፮፤ ማር. ፲፬፥፩-፲፩፤ ሉቃ. ፳፪፥፩፮፡፡

የአስቆሮቱ ይሁዳ እንደ ሌሎች ሐዋርያት ከጌታችን ተምሯል፡፡ በረከተ ኅብስቱን ተመግቧል፡፡ ልዩ ልዩ ተአምራት በጌታችን እጅ ሲደረጉ ዅሉ ተመልክቷል፡፡ ጌታችንም ከሌሎች ሐዋርያት ሳይለየው እግሩን አጥቦታል፡፡ ከዳተኛው ይሁዳ ግን ለሐዋርያነት የጠራውን፣ ተንበርክኮ እግሩን ያጠበውን ጌታ ለሞት አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ‹‹የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሔዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት!›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ማቴ. ፳፮፥፳፬)፡፡ ሌሎች ሐዋርያት ከጌታችን ዘንድ ፍቅሩን ገንዘብ ሲያደርጉ ይሁዳ ግን እርግማንን ነው ያተረፈው፡፡ ‹‹ገንዘብ የኃጢአት ሥር ነው፤›› ተብሎ አንደ ተነገረ የኃጢአት ሥር የተባለው ገንዘብ የክርስቲያኖችን ሕይወት ያዳክማልና ምእመናን እንደ ይሁዳ በገንዘብ ፍቅር እንዳንወድቅ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ሰው ‹‹ይህን ዓለ ቢያተርፍ ነፍሱን ከጐዳ ምን ይጠቅመዋል?›› ተብሎ የተነገረውን ቃል ልብ ማለት ጠቃሚ ነው፡፡

ክርስቲያን ነን በማለት የክርስትናውን ስም በመያዝ እምነታቸውን፣ የቆሙበትን ዓላማ በመገንዘብ የሚለውጡ ሰዎች ዛሬም እንደ ይሁዳ ጌታችንን እየሸጡት እንደ ኾነ ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ ለድሆች መመጽወት ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ ዳሩ ግን በድሆች ስም የሰውን ገንዘብ ለግል ጥቅም ማዋል እጅግ የከፋ ኃጢአት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ለገንዘብ ብለው ድሆችን ለረኃብ ለችግር ባልንጀራቸውን ለመከራ እና ለሞት አሳልፈው ሲሰጡ ምንም አይጸጽታቸውም፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን ሕይወታችንን ለገንዘብ ፍቅር ሳይኾን ለእምነታችንና ለባልንጀራችን አሳልፈን መስጠት ይኖርብናል፡፡ በፍቅረ ንዋይ ተጠምደን ሰዎችን አሳልፎ በመስጠት ለአይሁዳዊ ሸንጐ ምቹ ኾነን መገኘት እንደሌለብን መገንዘብ አለብን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *